"ከምርጫ ማግስት ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግስት" በሚል መሪ ቃል የ2018 የፓርቲ ስራዎች ግምገማና የ2019 የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
ሐምሌ 25/2018 ዓ.ም የሁልባራግ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት !
የሁልባራግ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት "ከምርጫ ማግስት ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግስት" በሚል መሪ ቃል የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ ስራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የፈጻሚ ማዘጋጃ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
መድረኩን በመግቢያ ንግግር የከፈቱት የሁልባራግ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሙላጎ ከይረድን፣ ጠንካራ መንግስት የሚገነባው በጠንካራ ፓርቲ መሆኑን ገልጸው፣ ብልፅግና ፓርቲም ለሀገራዊ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን በመቅረጽ የተሻለ አገር ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በንግግራቸውም ሀገሪቱ በምክክርና በመግባባት ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ለማጠናከር የብሔራዊ ምክክር ሂደት ጠቃሚ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፓርቲው በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለህዝብ የገባውን ቃል ለመፈጸም ባለፉት አምስት ዓመታት አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን አስታውሰዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ከተመዘገቡ ውጤቶች መካከል 7ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በስኬት ማከናወን እና ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ የወጡ የልማት ፕሮጀክቶችን ለህዝብ አገልግሎት ማብቃት ተጠቃሽ ስኬቶች መሆናቸው ተገልጿል። ሆኖም የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ይበልጥ በትኩረት መፍታት እንደሚገባም ተጠቅሷል።
አመራሩ የፓርቲ አደረጃጀቶች በሁሉም ደረጃ ተጠናክረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበው፣ በ67 ህብረቶች የቢሮ ግንባታና ስራ ማስጀመር ላይ የታዩ ክፍተቶች በውይይቱ ትኩረት አግኝተው እንዲፈቱ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመድረኩ ለውይይት መነሻ የሚሆን የ2018 የፓርቲ ስራዎች እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የሁልባራግ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊና የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ኑረድን መሀመድ እንዲሁም የ2019 የፓርቲ ስራዎች እቅድ ሰነድና የ2018 የቀበሌዎ የፓርቲ ስራዎች የምዘና ሪፖርት ሰነድ የሁልባራግ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካና ርዕዮተ አለም ዘርፍ ኃላፊና የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ የሁልባራግ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዲ አወል፣ የሁልባራግ ወረዳ ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ እንዳለ ፍቃዱ፣ የወረዳ አመራሮች፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የፓርቲ ኃላፊዎች፣ የህብረት ሰብሳቢዎች፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀት አመራሮች፣ የቀበሌ ስራስኪያጆች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመድረኩ የተገኙ ሲሆን በመጨረሻም ተሳታፊዎች የ2019 በጀት ዓመት የፓርቲ ስራዎች በተጠናከረ ቅንጅት እንዲፈጸሙ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ መድረኩ ተጠናቋል።